Dilla University STEM Center
Event

የዲላ ዩኒቨርሲቲ STEM ማዕከል ለክረምት ሰልጣኝ ተማሪዎች ገለፃ አደረገ።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ STEM ማዕከል ለክረምት ሰልጣኝ ተማሪዎች ገለፃ አደረገ።
አቶ ደረጄ ሾንጣ

የዲላ ዩኒቨርሲቲ STEM ማዕከል ለክረምት ሰልጣኝ ተማሪዎች ገለፃ አደረገ።

===========*******===========

ዲ.ዩ፡ ሐምሌ 26/2017ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)

በዩኒቨርሲቲው እስቴም (STEM) ማዕከል ስልጠና ለሚወስዱ 300 ተማሪዎች ነው ገለፃው የተደረገው። 

አዲሱ ፍርንጆ (ዶ/ር) የዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪ ግንኙነትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ባደረጉት ንግግር፣ ማዕከሉ በክረምት እንዲሁም በቅዳሜና እሁድ መርሐግብር ተማሪዎችን እየተቀበለ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ ተናግረው፣ በዛሬው ዕለትም አዲስ ለገቡ 300 የክረምት መርሐግብር ሰልጣኞች ገለፃ መደረጉን ገልፀዋል። 

ዶ/ር አዲሱ አያይዘውም የማዕከሉን አድማስ ለማስፋትና ይበልጥ ለማዘመን፣ በማዕከሉ ሰልጣኝ ተማሪዎችና መምህራን የለማ ድህረገጽ ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን፣ እንዲሁም የሮቦቲክ (Robotic )እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ስልጠና ለመስጠት አስፈላጊ ግብአቶች መሟላታቸውን ገልፀዋል።

አቶ ደረጀ ሾንጣ የጌዴኦ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ሀላፊ በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው የሳይንስና ፈጠራ ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎች፣ በጌዴኦ ዞን ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ ከ7ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ለተመረጡ 300 ተማሪዎች ያዘጋጀው ስልጠና፣ ተቋሙ ለቴክኖሎጂው ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ተማሪዎች በቆይታቸው የዩኒቨርስቲውን ስርዓት በማክበርና ትምህርታቸው ላይ ትኩረት በማድረግ ለቀጣይ ህይወታቸው ስንቅ ሊሆናቸው የሚችለውን የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት ይዘው እንዲወጡ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፣ አቶ ደረጀ።

የቀድሞ የማዕከሉ ሰልጣኝ ተማሪ ቸርነት አሳዬ የህይወት ተሞክሮውን ለአዳድስ ሰልጣኞች ያካፈለ ሲሆን፣ ከአራት ዓመት በፊት እስቴም ማዕከሉን በመቀላቀል ጥሩ ውጤት በማምጣትና ችግር ፈቺ ፕሮጀክት በመስራት ስልጠናውን ማጠናቀቁን ገልፆ፣  ለተለያዩ ድርጅቶችም የቴክኖሎጂ ስራዎችን እየሰራ ከእራሱም አልፎ ቤተሰቡን እያገዘ እንደሚገኝ ተናግሯል።

ሰልጣኝ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የመኝታ፣ የምግብና የሕክምና አገልግሎት እያገኙ ለሁለት ወር በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ዘርፍ፣ ተግባር ተኮር ስልጠና እንደሚወስዱ በመርሐግብሩ ተገልጿል።

በተመሳሳይ፣ በዛሬው እለት ላለፉት 3 ወራት በቅዳሜና እሁድ መርሃ ግብር በማዕከሉ ስልጠናቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ 37 ሰልጣኞች ተመርቀዋል።

===##===

#የአረንጓዴው_ምድር_ዩኒቨርሲቲ!

ዘገባዉ የዲላ ዩንቨርስቲ ህዝብ ግኑኝነት ነዉ።

Back to News